Friday, August 26, 2011

ማህበረ ቅዱሳንና አቡነ ጳውሎስ በመስማማት ላይ ናቸው


የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ከማኅበረ ቅዱሳን አመራር ጋር ውይይት አደረጉ አትም ኢሜይል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢተዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከማኅበረ ቅድሳን ሥራ አመራርና አስፈጻሚ ጉባኤያት ተወካዮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ስለ ማኅበሩ አገልግሎትና በተለይም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት በተካሔደው ውይይት፤ የማኅበሩ አመራር ስለተሐድሶ መናፍቃን እንቅቃሴ አራማጆችና ተቋማት የተዘጋጁ ልዩ ልዩ መጻሕፍት እንዲሁም በምስል ወድምጽ /VCD/ የታገዘ ገለጻና ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት ከተመለከቱ በኋላ “ይህ ሁሉ የንብ ሠራዊት እያለ ወረራው ሲካሔድ የት ነበራችሁ?” የሚል የአባትነት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር መጠበቅ የሁሉም ሓላፊነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህም በላይ መብታችንን በሕግ ሳይቀር ማስከበር እንደሚኖርብን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በልጅነት ደረሻው እያከናወነ ያለው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ “ተሐድሶ ናቸው” ማለት ግን አግባብ እንዳልሆነና ይህም የቤተ ክርስቲያናችንን አሠራር ጠብቆ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የማኅበሩ አመራር አባላትም፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ሥራ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነት፣ በእንዴት ዓይነት ሁኔታና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምእመናን ግንዛቤ አግኝተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ፤ እንዲሁም ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የሚመሩና የሚደግፉ ተቋማትን፣ ስልትና አሠራራቸውን የማሳወቅ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ1990 ዓ.ም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ የማጋለጥ ሰፊ ሥራ ባከናወነበት ወቅት፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ነገር ግን ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ በምእመኑ ውስጥ በመዝራት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው “መነኮሳት” ተወግዘው እንዲለዩ ሲደረግ፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐትና አሠራር መሠረት ማኅበሩ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ ለሊቃውንት ጉባኤ አቅርቦ ከዚያም በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረገበት ሁኔታ እንደነበረ፤ የማኅበሩ አመራር አባላት በውይይቱ ላይ አስታውሰው፤ ማኅበሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር ጠንቅቆ እንደሚያውቅና ይህንኑ ለማስጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ማኅበረ ቅዱሳን እየሠራ ያለው የግለሰቦችን ስም በመጥቀስ “ተሐድሶ” የማለት ሳይሆን፤ ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነትና ስልት ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ምእመናን ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማሳወቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ወደፊትም በዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና ሥራ ላይ የተጠመዱ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ የሚገኙ አካላትንና ደጋፊዎችን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር በመጠበቅ ማኅበረ ቅዱሳን ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትና አባቶች እንደሚያቀርብ በማኅበሩ አመራር አባላት ለቅዱስነታቸው ተገልጿል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩም፤ በበቂ መረጃ በማስደገፍ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አካል በማቅረብ ሁሉም ነገር በሕግና በሥርዐት መከናወን እንዳለበት አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስለ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ ጉዳይ በሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ሰላም የሰጠው ቃለ ምልልስ

ስለ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ያስተላለፈውን መልዕክት እነሆ!!! ምንጭ (ደጀ ሰላም)

ስለ ተሐድሶ እና ተያያዥ ጉዳዮች የዘሪሁን ሙላቱ ቃለ ምልልስ


“የሃይማኖታችን ጉዳይ የፓትርያርኩ ብቻ አይደለም” የሚለው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ከቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ  የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ መለኮት፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በፊሎሎጂ ትምህርት ተመርቋል። በአሁኑ ወቅትም ደግሞ የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ) ጥናቱን በማገባደድ ላይ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ወቅታዊ ሁኔታ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትከተለው አስተምህሮ ዙሪያ ከዕንቁ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
 
 
ከዚህ በታች ያለውን ሙሉ ቃለ መጠይቁን እንድታነቡ በአክብሮት እንጠይቃለን!!!

ብፁእ አቡነ ሚካኤል አረፉ

ስለ "ብፁዕ አቡነ ሚካኤል" የማ/ቅዱሳን ዘገባ

(Mahibere Kidusan):- የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ነሐሴ 8 ቀን 2003 ዓ.ም አርፈዋል። በአንብሮተ ዕድ ከተሾሙበት ከነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ በአሁኑ ሀገረ ስብከታቸው የተሾሙ ሲሆን በመካከል ለተወሰኑ ወራት የወላይታ፣ ዳውሮና ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።

የሐሞት ጠጠር ሕመም የነበረባቸው ብፁዕነታቸው የቀዶ ጥገና ሕክምናቸውን በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በመከታተል ላይ የነበሩ ሲሆን በመካከል ከሰመመናቸው መንቃት ሳይችሉ እንደቀሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ቀጣይ የአስከሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ምክንያቱ ሊገለጽ እንደሚችልም ይገመታል።

በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የተሾሙት የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት አባ ተክለ ሚካኤል ዓባይ አሁን ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በቀድሞው አድዋ አውራጃ በዓምባ ሰነይቲ ወረዳ በላውሳ ቅዱስ ገብርኤል አካባቢ ከአለቃ ዓባይ ወ/ገብርኤልና ከወ/ሮ ታደለች ንጉሤ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

በታላቁ በደብረ ዓባይ ገዳም ከመምህር አበራና ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ከመሠረተ ትምህርት እስከ ጸዋትወ ዜማ፣ ከመምህር የኔታ የኋላእሸት መዝገበ ቅዳሴ ጠንቅቀው ከተማሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

በዋልድባ ገዳም መዓርገ ምንኩስና ተቀብለዋል፡፡ ጎንደር ክፍለ ሀገር በወገራ አውራጃ በጉንተር አቦ ከመሪጌታ ሐረገወይን፣ ጎንደር ከተማ ከመምህር እፁብ ቅኔ ተምረው ተቀኝተዋል፡፡

በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እያገለገሉ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት በአዳሪነት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በውጪ አገር እንግሊዝ ለንደን ሴንት ኤድዋርድስ ኮሌጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለአንድ ዓመት፣ ግሪክ አገር በአቴንስ ዩኒቨርስቲ ለስድስት ዓመታት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር በቲኦሎጂ ማስትሬት ዲግሪ፣ በአሜሪካ ሆሊ ክሮስ በተባለው የግሪክ ሴሚናሪ ከሲስተማቲክ ቲኦሎጂ ዲፕሎማ፣ በቦስተን ዩኒቨርስቲ የኤስ.ቲኤም ወይም በፓስተራል ካውንስሊንግ /ሳይኮሎጂ/ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የእስኮላር ሽፕ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ ገዳማት መምሪያ ኃላፊ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ዲን፣ በወቅቱ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የዕቅድና ጥናት መምሪያ ኃላፊ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሐላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ ነሐሴ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና እንግዶች እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።