Friday, August 26, 2011

ማህበረ ቅዱሳንና አቡነ ጳውሎስ በመስማማት ላይ ናቸው


የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ከማኅበረ ቅዱሳን አመራር ጋር ውይይት አደረጉ አትም ኢሜይል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢተዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከማኅበረ ቅድሳን ሥራ አመራርና አስፈጻሚ ጉባኤያት ተወካዮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ስለ ማኅበሩ አገልግሎትና በተለይም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት በተካሔደው ውይይት፤ የማኅበሩ አመራር ስለተሐድሶ መናፍቃን እንቅቃሴ አራማጆችና ተቋማት የተዘጋጁ ልዩ ልዩ መጻሕፍት እንዲሁም በምስል ወድምጽ /VCD/ የታገዘ ገለጻና ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት ከተመለከቱ በኋላ “ይህ ሁሉ የንብ ሠራዊት እያለ ወረራው ሲካሔድ የት ነበራችሁ?” የሚል የአባትነት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር መጠበቅ የሁሉም ሓላፊነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህም በላይ መብታችንን በሕግ ሳይቀር ማስከበር እንደሚኖርብን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በልጅነት ደረሻው እያከናወነ ያለው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ “ተሐድሶ ናቸው” ማለት ግን አግባብ እንዳልሆነና ይህም የቤተ ክርስቲያናችንን አሠራር ጠብቆ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የማኅበሩ አመራር አባላትም፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ሥራ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነት፣ በእንዴት ዓይነት ሁኔታና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምእመናን ግንዛቤ አግኝተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ፤ እንዲሁም ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የሚመሩና የሚደግፉ ተቋማትን፣ ስልትና አሠራራቸውን የማሳወቅ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ1990 ዓ.ም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ የማጋለጥ ሰፊ ሥራ ባከናወነበት ወቅት፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ነገር ግን ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ በምእመኑ ውስጥ በመዝራት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው “መነኮሳት” ተወግዘው እንዲለዩ ሲደረግ፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐትና አሠራር መሠረት ማኅበሩ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ ለሊቃውንት ጉባኤ አቅርቦ ከዚያም በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረገበት ሁኔታ እንደነበረ፤ የማኅበሩ አመራር አባላት በውይይቱ ላይ አስታውሰው፤ ማኅበሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር ጠንቅቆ እንደሚያውቅና ይህንኑ ለማስጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ማኅበረ ቅዱሳን እየሠራ ያለው የግለሰቦችን ስም በመጥቀስ “ተሐድሶ” የማለት ሳይሆን፤ ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነትና ስልት ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ምእመናን ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማሳወቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ወደፊትም በዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና ሥራ ላይ የተጠመዱ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ የሚገኙ አካላትንና ደጋፊዎችን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር በመጠበቅ ማኅበረ ቅዱሳን ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትና አባቶች እንደሚያቀርብ በማኅበሩ አመራር አባላት ለቅዱስነታቸው ተገልጿል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩም፤ በበቂ መረጃ በማስደገፍ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አካል በማቅረብ ሁሉም ነገር በሕግና በሥርዐት መከናወን እንዳለበት አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

1 comment:

  1. እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን አሜን!!!

    ReplyDelete