Sunday, October 9, 2011

የጌታችን ክህነትና የመልከ ፄዴቅ ክህነት



ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ጠቀሰው? - - - ዕብ.3:1 “ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በእብራውያን መልእክቱ ያተኮረው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ማስረዳት ነው፡፡ ይህንንም የሚያስረዳው ደግሞ በንፅፅር ነው፡፡ ከነቢያት ስለመብለጡ የእነሱን ንግግርና የእሱን ንግግር በማነፃፀር አስረዳ፡፡ ከዚያም በኅላ ደግሞ ከመላእክት መብለጡን አስረድቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከካህናት መብለጡን ለማስረዳት ያመጣል፡፡ ከካህናት መብለጡንም ሲያስረዳ ዋናወቹ ምክንያቶች 1) በክህነቱ 2) በመስዋእቱ 3) መስዋእቱ በቀረበበት ድንኳን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለክህነቱም በ ዕብ.5፡1-10 ፣ በዕብ. 6፡20 ፣ 7፡1-28 ፣ 8፡1-3 ባሉት አስረድቷል፡፡

ክህነት ምንድን ነው? - - - አገልግሎት ሲሆን መሾምን መመረጥን ያመለክታል፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስም ከአዳም ጀምሮ የተለያዩ ሰወች ለዚህ ክህነት በሰውም በእግዚአብሄርም ሲመረጡ ያሳየናል፡፡ 

መልከ ፄዴቅ ማነው? - - ዕብ.7:3 “አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ይህ ሲባል መልከ ፄዴቅ ሰው አይደለም ማለት አይደለም ፡ ዘሩ ከካም ዘር ነበረና በሙሴ መፃህፍት አልተገለፀም ለማለት ነው፡፡ ይህ የተመረጠ ሰው አፅመ አዳምን እንዲጠብቅ የታዘዘ በብህትውና የሚኖር ነው፡፡ የመልከ ፄዴቅ ክህነትም ሙሴ አሮንን በሾመበት ሥርአት ቅብዕ አፍልቶ ፡ መስዋእተ እንስሳ ሰውቶ ፡ልዩ ልዩ ህብር ያላቸውን አልባሳት አልብሶ የሾመው ሰው የለም፡፡ይልቁንም እግዚአብሄር መረጠው ፡ በማይታወቅ ግብርም ሾመው እንጂ፡፡ አሮንና ልጆቹ በሙሴ እጅ ፡ ሙሴም በመልአኩ እጅ እንደተሾሙ (ሐዋ ፡ 6፡6) መልከፄዴቅ ግን ሹመቱ ከእግዚአብሄር ነውና ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ያለው ለዚህ ነው፡፡ “ለዘላለም” ማለቱም እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ማለቱ ነው፡፡በዚህም ምክንያት ክህነቱ ከሌዋውያን ክህነት ፍፁም የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንደሌዋውያን ክህነትም የእንስሳት መስዋእት አይሰዋም መስዋእቱ ንፁህ ስንዴና ወይን ነውንጂ፡፡ በዚህም ተነስቶ ቅዱስ ጳውሎስ - - ዕብ.7:11 እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ብሎ ይጠቅሰዋል፡፡
ነገር መልከ ፄዴቅ በእብራውያን - - -

  1. የሌዋውያን ካህናትን በክህነት ይቀድማቸዋል እርሱ ከአብርሃም በፊት ነበረና --- ዘፍ 14፡18-21 
  2. ክህነቱ ዘላለማዊ ነው - ዕብ 7፡3 ለብዙ ዘመናት በብህትውና እንደኖረና ክህነቱም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ስላልሆነ ይህ ተጠቅሷል፡፡ የሌዋውያን ክህነት ግን ሞት በየጊዜው አለባቸውና ዕብ.7:23 “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው” እንዲል፡፡ 
  3. ሌዋውያንን አስራት አስወጥቷል - - - ሌዋውያን ከህዝቡ አስራትን እንዲቀበሉ ስርአት አላቸው፡፡ ነገር ግን መልከ ፄዴቅ ከአብርሃም አስራትን በተቀበለ ጊዜ ከእነርሱ ክህነት የእርሱ ክህነት እንዲበልጥ ታወቀ፡፡ 
  4. ሌዋውያንን ባርኳል - - - እጃቸውን ዘርግተው ህዝቡን የሚባርኩት የሌዋውያን ካህናት በአብርሃም በኩል በመልከ ፄዴቅ ተባርከዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.7:6-7” ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል።ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው።”እንዲል፡፡ 
  5. መስዋእቱ የሚሞቱ እንስሳት አይደሉም - - - የሌዋውያን ካህናት መስዋእታቸው ከእንስሳት የሚዘጋጅ ሲሆን የመልከፄዴቅ መስዋእት ግን ከንፁህ ስንዴና ወይን የሚዘጋጅ ነው ፡፡ ይህም የክርስቶስ ስጋውና ደሙን የሚያመለክትልን ነው፡፡ 

ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉንም በዚህ ምእራፍ አጠቃልሎ እንዳስቀመጠው ክህነተ መልከፄዴቅ ክህነተ ሌዋውያንን ይበልጣል፡፡ የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክህነት ደግሞ ከመልከ ፄዴቅ ክህነት ይበልጣል፡፡ መልከፄዴቅ ለጌታችን አምሳል ነበርና፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር አባታችሁ አብርሃም አብርሃማዊ ካልሆነው ከመልከ ፄዴቅ የሚያንስ ከሆነ ይልቁንም ከመልከ ፄዴቅ አምላክ ከክርስቶስማ እንዴት አያንስም? የመልከ ፄዴቅ ክህነት ከእናንተ ከተሻለ ይልቁን የጌታማ እንዴታ! መስዋእታችሁ ከመልከ ፄዴቅ ካነሰ ይልቁን እንዴት ከጌታ ትበልጣላችሁ ፣ ለመልከ ፄዴቅ አስራት ካወጣችሁ ለጌታማ እንዴት አብዝታችሁ ማድረግ አይገባችሁ? በመልከ ፄዴቅ ከተባረካችሁ ይልቁንም መስጠትና መንሳት ለእርሱ ብቻ ከሚቻለው ከወልደ እግዚአብሄርማ እንዴት አብልጣችሁ መጠቀም ይገባችኅል ለማለት ተናገረው፡፡አላማውም የጌታን ታላቅነትና የባህርይ አምላክነት በመመስከር ልቆ ከሚልቁት እነርሱንም ያላቃቸው እርሱ መሆኑንና ይህ ስልጣን እንዳለው ለማስታወቅ ነበር፡፡

የጌታችን ክህነት በምን የተለየ ሆነ? - - -

  1. የባህርይው ስለሆነ - - - ክርስቶስ ሁሉንም ነገር ያደረገው በስልጣኑ ነው፤ ሙትን ያስነሳው ድውያኑን የፈወሰው ፡ ያስተማረው ፡ የሞተው ፡ የተነሳው ፡ ያረገው ፡ - - - በስልጣኑ ነው፡፡ የጌታችን የክህነት አግልግሎት ዋናው ራሱን በመስቀል ላይ መስዋእት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይሄውም ስጋውን ቆርሶ ፡ ደሙን አፍስሶ ፡ ነፍሱን ክሶ አለሙን የመቀደስና የማንፃት ሞትንና የሞትን አበጋዝ ዲያቢሎስን በሞቱ ድል መንሳቱ ነው፡፡ ይህ ነው የጌታችን ከእርሱ ለእኛ የተደረገልን የክህነት አገልግሎት፡፡ ሞቱ ደግሞ በስልጣኑ እንደሆነ ሞቱን በስልጣኑ ፈፀመው መባሉ ደግሞ ክህነቱ የባህርይው መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከማንም አልተቀበለውም ፡ ማንምም ከእርሱ አይወስድበትም፡፡ይህም ማለት ባህርይ መለኮቱ ባህርይ ትስብእቱን በተዋህዶ አከበረው እንጂ ሌላ የሚሰጠው እርሱም የተቀበለው የለም፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደመልከፄዴቅ በስውር እንደ አሮን በገሃድ የተሾመ አይደለም ፡ እርሱ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለምና፡፡ዮሐ 1፡3 “ሁሉ በእርሱ ሆነ” እንዲል፡፡ ዕብ.5:5 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው” ሲል የቃልን በስጋ መወለድ ሐዋርያው ተናግሯል፡፡ ይህም በእርሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆነ በአባቱም ፈቃድ መሆኑን ለመናገር ነው፡፡ 
  2. ዘላለማዊ ነው - - - “ዘላለም” የሚለው ቃል ለፍጡርና ለፈጣሪ ሲቀፅል አንድ እንዳልሆነ አንባቢ ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህም የመልከፄዴቅ ክህነት ህይወቱ እስኪያልፍ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የጌታችን ክህነት ዘላለማዊነቷ እርሱ ሽረትና ሞት የሌለበት አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ በስጋ ሞተ የምንለውም ነፍሱ ከስጋው ተለየች ለማለት እንጂ ከተዋህዶ በኅላ መለኮትና ትስብእት የተለያዩበት ቅፅበት የለም፡፡ስለዚህ ለክህነቱ ተቀባይ አያስፈልገውም ፡ የባህርይ ክህነትም ከእርሱ በቀር ገንዘብ ሊያደርገው የሚቻለው የለምና፡፡ ዕብ.7:24 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው” ተብሎ ተፅፏልና፡፡ዕብ.7:24-25 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” - - - እነዚህ ጥቅሶች ጌታችንን “አማላጅ” ነው በማለት የሚያስተላልፉት መልእክት የለም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት አምነው ሲመጡ የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ ሆኑ የሚባሉት በስመ ስላሴ ተጠምቀው የክርስቶስን ስጋና ደም ሲቀበሉ ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስ ስጋና ደም ደግሞ እንደ ኦሪት መስዋእት በአንድ ቀን የሚያልቅ ፡ በጊዜ ብዛት የሚለውጥ ፡ የሚበላሽ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ አዲስና ለዘላለሙ በህይወት የሚኖር ነው፡፡ “ሕያው” መባሉም ነፍስ ስለተዋሃደው ሳይሆን “መለኮት” ስለማይለየው ነው፡፡ - - - ይህ ሕያው ስጋውና ደሙ ሁልጊዜ ሰውን ወደ እግዚአብሄር ሲያቀርብ የሚኖር ከእግዚአብሄርም ጋር የመታረቂያው ብቸኛ መንገድ በመሆኑ አማለደን (አስታረቀን) ሲል ገልፆታል፡፡ “ሊያማልድ በህይወት ይኖራል” የሚለውንም በጥሬ ንባቡ ከሆነ ጌታችን አሁንም በስጋ ህይወት በምድር አለ ያስብልብናልና፡፡ 
  3. ፍፁም ነው - - - የሌዋውያን ክህነት ፍፁም አይደለም ፤ የመልከ ፄዴቅም ዘላለማዊ እንጂ (አንፃራዊ) ፍፁም አልነበረም፡፡ ማንንም ወደ ገነት መመለስ አልተቻላቸውምና፡፡ እነርሱም ራሳቸው በአዳም የመጀመሪያ ሃጢአት ተይዘዋልና፡፡ “እርሱ ራሱ ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ” ዕብ 7፡28 ፣ ዕብ 5፡2 ተብሎባቸዋልና፡፡ ለጌታችን ግን ሃጢአት የለበትም ተብሏል፡ 1ኛ ዮሐ3፡5 ከዚህ የተነሳ ክህነታቸው ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 እርሱ ግን ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ቆላ.1:19-20 “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።”እንዲል 

ታዲያ የጌታችን ክህነት በመልከ ፄዴቅ ክህነት ለምን ተመሰለ?

“የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10፡1 እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ ፡ የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16፡4 ፣ ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 3፡14 ፣ ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10፡1 እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡ በመልከ ፄዴቅ የመሰለበት ምክንያትም

የመልከ ፄዴቅ እናትና አባት በእብራውያን ዘንድ የታወቀ እንዳልሆነ የጌታችን ለቀዳማዊ ልደቱ እናት ለደሃራዊ ልደቱ አባት የለውምና 
መልከ ፄዴቅ በስንዴ በወይን ያስታኩት ነበረ ፤ ጌታም ቅዱስ ስጋውን በስንዴ ክቡር ደሙን በወይን አድርጎ ሰጥቶናልና 
መልከ ፄዴቅ በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም አለፈ አይባልም ፤ ጌታም በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም ያልፋል አይባልም፡፡ እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ጌታችን ስለምን ሊቀካህናት ተባለ?

ከላይ በመልከ ፄዴቅ እንደተመሰለ አሁን ደግሞ በኦሪት ሊቀ ካህናት ተመስሏል፡፡ ስለ ምን? ስለጌታችን ክህነት የመልከ ፄዴቅ ምሳሌነት ያልገለጠው ነገር አለ ፤ ይሄውም አገልግሎቱ ነው፡፡ ጌታችንም ሊቀ ካህናቱን ምሳሌ ያደረገው ከዚህ አገልግሎቱና ከአለቅነቱ አንፃር ነው፡፡ ይሄውም ፦

  1. ሊቀ ካህናት ከሰው ተመርጦ ለሰው ይሾማል - - - ዕብ.5:1 “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና” እንዲል፡፡ ሊቀ ካህናት ሰው ነው ፡ ከሰው ይመረጣልና የሚሾመውም ለሰው እንጂ ለራሱ ክብር አይደለምና፡፡ ጌታችን ክርስቶስም ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ የዳዊት ልጅ ተብሏልና፡፡ማቴ 1፡1 ሊቀ ካህናት ስለሰው እንደሚሾም ጌታችንም ሰው የሆነውና ክህነትን ገንዘብ ያደረገው ስለ ሰው ነው፡፡ የሰውን ሃጢአት ለማራቅ ሰው ሆኗልና፡፡ዮሐ.3:16-17 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” 1ጢሞ.1:15 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” እንደተባለ፡፡ 
  2. ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናት ብቻ ነው - - - ይህንንም በዘሌ16፡2 የተጠቀሰውን ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.9:6-7 “ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል፡፡ ጌታችንም የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን በሰው ያልተተከለች በፈቃደ እግዚአብሄር የሆነች ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኅላ ማንም ያልገባባትና የማይገባባት ናት፡፡ ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ ይገባል ፡ እርሱ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ገባ ፤ ለዓለምና ለዘላለም መስዋእቱ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እነዚያ በየዓመቱ የሚገቡት ሟች ስለሆኑ መስዋእታቸውም ሙት ነውና ሌላ አዲስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ዕብ.9:11-12 “ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ተብሎ ተፅፏል፡፡ ጌታችን የገባባት ድንኳን የተባለችው “መስቀል” ናት፡፡ ድንኳን ያላት የዘላለም መስዋእት የሆነው የጌታ ቅዱስ ስጋ የተቆረሰው ክቡር ደሙም የፈሰሰው በመስቀሉ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚች ድንኳን “አንድ ጊዜ ፈፅሞ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገባ” በማለት ራሱን መስዋእት አድርጎ የወጣበት መስቀል መሆኑን በግልፅ አስረድቷል፡፡ “በሰው ያልተተከለች” ሲልም አይሁድ መስቀሉን ጌታን ለመግደል እንጂ መስዋእተ እግዚአብሄር ይቀርብበታል ብለው ስላልሆነ ነው፡፡ “ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች” ማለቱም በመስቀል ላይ እራሱን መስዋእት ሊያደርግ የሚችል ሰው የለም ፤ ቢኖርም እንኳ ሌላውን ራሱን ማዳን አይቻለውምና ፡ ለፍጥረት ባልሆነች ብሏታል፡፡ 
  3. ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መስዋእትን ሊያቀርብ ይሾማልና ዕብ 8፡3 -- -- የሊቀ ካህናት ዋናው አገልግሎት መባንና መስዋእትን ማቅረብ ነው፡፡ ጌታችንም የዓለምን ሃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ የተባለበት ዮሐ1፡29 ራሱን መስዋእት አድርጎ ያቀረበ ብቸኛ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ራሱ መስዋእት በመሆኑም ሌላ የሚያቀርበው መስዋእት አላስፈለገውም፡፡ ሁለቱንም አንድ ጊዜ መሆን ይቻለዋልና፡፡ ዕብ.9:12 “የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ዕብ.10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” እንዲል፡፡ ዕብ.9:26 “- - - አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ዕብ.8:1-3 “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” ሲለን የትሩፋተ ስጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪ በልእልና ሃይል ባለው እሪና የተቀመጠ አስታራቂያችን ነውና ስለዚህ ተናገረ አንድም የዚህ ሁሉ ደገኛ ነገሩ ሊቀ ካህናታችን በልእልና ሃይል ባለው እሪና የኖረው መኖርን ይገልፃል፡፡ “እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” የተባለውበሰው ፈቃድ ያይደለ በእግዚአብሄር ፈቃድ በተተከለች በደብተራ መስቀል ራሱን መስዋእት ፡ መስዋእት አቅራቢውም ራሱ ደግሞም መስዋእቱንም ተቀባይ ራሱ ሆኖ ለቅዱሳን ሲያገለግል ኑሮ ነበር፡፡ የክርስቶስ መስዋእትም “ሕያው” ማለትም ለዘላለም የሚኖር ሲሆን እንደ ሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ ቶሎ የሚበላሽ ስለዚህም እለት እለት መስዋእት ማቅረብ የሚገባበት አይደለም፡፡ የቀደሙት ሊቀካህናት በሰው በተተከለችው ቅድስተ ቅዱሳን በአመት አንድ ጊዜ መስዋእትን ሊያቀርቡ እንደሚገቡ ያይደለ ለክርስቶስ ግን በእግዚአብሄር በተተከለች ደሙን ባፈሰሰባት ፡ ስጋውን በቆረሰባት ፡ ነፍሱን ካሳ አድርጎ በሰጠባት እውነተኛይቱ መቅደስና ድንኳን በተባለች በመስቀል አንድ ጊዜ ፈፅሞ ገባ ማለት ተሰቀለ፡፡ መስዋእቱን ያቀረበው ክርስቶስ የቀረበው መስዋእት የክርስቶስ ክቡር ስጋው ቅዱስ ደሙ ስለሆነ መስዋእት አቅራቢው እንደሌሎቹ ሊቀካህናት በራሱ ህፀፀ የለበትምና መስዋእቱም የሚበላሽ ፡ የሚሞት ፡ የሚበሰብስ እንደሆነው የቀደመው መስዋእት አይደለምና ነገር ግን ነገር ግን ለዘላለም የሚኖር ክርስቶስ ራሱን መስዋእት አድርጓልና የማስታረቁ ተግባር ፍፁም ነው፡፡ እርሱም ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ይህንን አንድ ጊዜ ፈፅሞ አድርጓልና፡፡ ክቡር ደሙና ቅዱስ ስጋውም ለዘላለም አምነውና በስላሴ ስም ተጠምቀው የሚመጡትን ሰወች ከሃጢአታቸው አጥቦ የዘላለም ህይወትን ሊያወራሳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ አንድም ዘወትር (አሁንም) መስዋእትን በሰማይ ያቀርባል ካልን እለት እለት በሰማያት ክርስቶስ ወደ እውነተኛይቱ ድንኳን (መስቀል) ይወጣል ማለት ይሆንብናል (ይህም ይሰቀላል ማለታቸን ነው) - - - ደግሞም የክርስቶስ መስዋእት እንደሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት ድካም አለበት ፍፁም አይደለምና አንድ ጊዜ የሰዋው መስዋእት አልበቃውም ማለት ይሆንብናል፡፡ - - - ሌላም ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰዋው መስዋእት ሙሉውን የሰው ልጅ እዳ በደል አላቀለለም ማለት ይሆንብናል፡፡ ይህም ሊባል አይገባም ክርስቶስም አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ሰውን ሁሉ ይቅር ብሏል ፡የማስታረቅንም ተግባር ፈፅሟል በሰማያትም በአባቱም ቀኝ ተቀምጧል ይህም መቀመጡን እንጂ ለአገልግሎት መቆሙን አያሳይም፡፡ ክርስቶስም ለሃዋርያቱ እንደተናገረ ውደ አባቴ የምሄደው አሁን እንዳደረኩ ስለሃጢአታችሁ ላማልድ አይደለም ይልቁንም ልፈርድ እንጂ በማለት ማማለድን በምድር እንደፈፀመው በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጦም የሚፈርድ እርሱ እንደሆነ አስቀድሞ ተናገረን፡፡ ይህንንም ዮሐ.16:26 “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም” ብሎ አስረግጦ ተናገረ፡፡ 

በአጭር ቃል ጌታችን ሊቀ ካህናት ሊባል የተገባው ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ በእውነተኛይቱ ሰው በማይገባባት ቅድስተ ቅዱሳን (መስቀል) አንድ ጊዜ ብቻ ስለገባ ፡ በእርሷም እውነተኛውን መስዋእቱን (ራሱን) ስላቀረበና ሃጢአተ አለምን ስላራቀ ነው፡፡ የቀደመው ክህነት ግን ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 ጌታችን ግን ክህነቱ ”ፍፁም” መሥዋእቱም “ህያው” ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ምንጭ፦ “ሁለቱ ኪዳናት” በእብራውያን መልእክት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተ


የአብ ፍቅር የወልድ ቸርነት የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

Tuesday, August 30, 2011

መምህር ግርማ ታገዱ

  • ድቁና እንጂ ቅስና የለኝም በማለታቸው ታግደዋል - ሊቀጳጳስ አባ ቆውስጦስ
  • ማስረጃ በማቅረቤ እግዱ ተነስቶልኛል - መምህር ግርማ
  • በድቁና የሚያገለግል ሰው ይላላካል እንጂ አያጠምቅም
  • እኔ ቅስናዬን ደብቄ ነው

ከስርዓት ውጭ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በርካታ ሰዎችን ፀበል አጠምቃለሁ እያሉ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ቤት ገዝተዋል የሚል ቅሬታ የቀረበባቸው መምህር ግርማ ወንድሙ፤ የ1.5 ሚ. ብር መኖሪያ ቤትና ፒክአፕ መኪና ያገኘሁት በስጦታ ተገዝቶልኝ ነው ብለዋል - መምህር ግርማ”
ቪሲዲ፣ ጋዜጣና መጽሔት ምር የመምህር ግርማ ነው እየተባለ በየቤተክርስትያኑ ሲሸጥ አይተናል የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች፤ በቤተክርስትያን ብቻ ሳይሆን በቤታቸውም ፀበል አጠምቃለሁ እያሉ ከምዕመናን ብር ይሰበስባሉ በማለት ይተቻሉ፡፡ ከስርዓት ውጭ በሆነ መንገድ በሚሰበስቡት ብር፤ የ1.5 ሚ.ብር ቤት፤ ፒክአፕ መኪና፤ ሚኒባሶችና ሌሎች ንብረቶችን አካብተዋል ይላሉ - ቅሬታ አቅራቢዎች፡፡

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት 12 የሰንበት ት/ቤቶች ባቀረቡት ቅሬታ፣ መምህር ግርማ የሚያካሂዱት የማጥመቅ ስራ ስርዓት የጣሰ ስለሆነ ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ረዳትና የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ቆውስጦስ፤ መምህር ግርማ ላይ እገዳ የተጣለው ቅስና የሌለው ሰው ማጥመቅ ስለማይችል ነው ብለዋል፡፡ በድቁና የሚያገለግል ሰው ይላላካል እንጂ አያጠምቅም  የሚሉት አባ ቆውስጦስ፤ በአቶ ግርማ ላይ ቅሬታ ስለቀረበ ጠርተን ስናናግራቸው፤ ድቁና እንጂ ቅስና የለኝም  በማለታቸው ሊታገዱ ችለዋል ብለዋል፡፡

መምህር ግርማ በበኩላቸው እኔ ቅስናዬን ደብቄ ነው እንደዚያ ያልኩት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጥያቄ የቀረበልኝ በቁጣ በመሆኑ ቅስና የለኝም ብዬ ተናግሬያለሁ የሚሉት መምህር ግርማ፤ አሁን ማስረጃ በማቅረቤ እግዱ ተነስቶልኛል ይላሉ፡፡ አቡነ ቆውስጦስ ግን እግዱ አልተነሳም ብለዋል፡፡ አቶ ግርማ እግዱ ከተወሰነባቸው በኋላ ቅስና ስላለኝ እግዴ ይነሳልኝ የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር የሚሉት አቡነ ቀውስጦስ፤ እኛ ሀሜትና ወሬን በመከተል ሳይሆን፤ በህጋዊ መንገድ ጠይቀን የደረስንበት ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡

 በመምህር ግርማ ንብረት ላይ ስለሚሰነዘረው ቅሬታ ተጠይቀው፤ ስለሌላው ጉዳያቸው እኛ አያገባንም ብለዋል አቡነ ቀውስጦስ፡፡ መምህር ግርማ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊትም መተተኛ ነው፣ አስማተኛ ነው የሚል አሉባልታ እየተወራብኝ ነበር፤ ያ አልሳካ ሲላቸው ቅስና የለውም ተብያለሁ ይላሉ፡፡ አሁንም በሥራ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ ማንም በአሉባልታ ከምወደው ምዕመን አይለየኝም የሚሉት መምህር ግርማ፤ንብረታቸውን በተመለከተ በሰጡት መልስ የውጪ ተመራማሪና የጆርጅ ቡሽ አማካሪ የነበሩ ግለሰብ ሲፈወሱ በ1.5 ሚሊዮን ብር ቤትና ፒካፕ መኪና ተገዛልኝ፤ ይሔ ስጦታዬ ነው፤ ወሬኞች ግን ካቻማሊና ሚኒባስ አለው ብለው ያስወራሉ ብለዋል፡፡

"ማለዳም። ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?"- ማቴ 16:3 

‹‹ሐሰት አንናገርም፤ እውነትንም አንደብቅም››
From Addis Admas

‹‹ ፋሽስት ጣልያን አሽቀንጥሮ የጣለልንን ቀንበር መልሰን አንሸከምም ››መምህር ተስፋዬ ሸዋዬ



  • ስልጣነ ክህነት የሚያላብስ ሊቀጳጳስ አሁንም በመንበር ላይ የለም 
  • ፋሽስት ጣልያን አሽቀንጥሮ የጣለልንን ቀንበር መልሰን አንሸከምም 
  • …..በ 1974 ዓ.ም ዶክተሮቹ ጳጳሳት ደካማውን ፓትርያልክ አንከርፍፈው ሮም ወስደው ለፓፓው አሰግደው…….‹‹ ውይ እዚህው ድረስ እንዲያው ደከማችሁ እዛው ካርዲናል ሾሜላችሁ የለም እንዴ እዚያው በማሰልጠን ትምህርት አመሳስሉ›› ተብለው መመሪያ ተቀበሉ 
  • የቤተክርስትያን ሐብቷ ሰው እንጂ ገንዘብ አይደለም 
  • አሁን በቤተክርስትያን ቁንጮ ላይ ሆነው የሚራኮቱት በአሜሪካ በራሽያ በሩማንያ የተማሩ እርስ በርሳቸው የሚናናቁ ናቸው 
  • የተዋህዶ ሐይማኖታችን እምነትና ትምህርት አይለወጥብንም ስርዓታችን አይናወጥብንም መቅደሳችን አይደፈርብንም የሚለው እንቅስቃሴ ለራስ ገፅታ ግንባታ ለማዋል መራወጥ ይታያል፡፡ 
  • ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት 1600 ዓ.ም በተጠንቀቅሰ ሲጠብቁ ኖረዋል አሁን ግን የተባለው ሊፈፀም ግድ ስለሆነ የማይቀር ነውና ምዕመኑ ሊሸበር አይገባም 
    ሊቅነት መንፈሳዊነት ነው ብለው ያምናሉ 
    ሊቅነት ከመንፈሳዊነት ጋር ግንኙነት የለውም ፡፡ መንፈሳዊነት ፤ ትህትና ፤ ትዕግስትን ፤ ፍቅርን ፤ ርህራሄን፤  ደስታን ፤ ሰላምን ፤ የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትን ሁሉ የተላበሰ መሆን ነው፡፡ ሊቅነት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው
  • ....ባንድ በኩል በተለያዩ ፓርቲዎች ፖለቲካ የተጠመዱ አባላት ይዞ የጳጳሱን የአቡኑ ቀሲሱንም ስራ እኔ ልስራ ማለት ስርዓተ ቤተክርስትያን መጠበቅን አያመለክትም ፡፡ 
  • ……አስተማርናቸው ያሏቸውን ምናልባትም ባለሰንሰለቱ ሳይሆን ታጣፊውን ታንክ እስከ ትከሻቸው እስከመያዝ ይታመኑናል ብለው የሚያስቧቸውን ለአደጋ አጋልጠው ቤተክርስትያን ሊያደኽይዋት ይችላሉ፡፡ 
  • መናፍቃንን በመለፍለፍ ወይም በስለላ እና በዱላ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ያውም እነሱ ጫማ ስር ተደፍቶ፡፡ የቃለ እግዚሐብሔርን እቃ ጦር ለብሶ የመንፈስ ቅዱስን ሰይፍ ታጥቆ በቀናች በተዋህዶ ሐይማኖት ፀንቶ በምሳሌነት በመቆም እንጂ 



(ከአምደ ሃይማኖት)

‹‹ቤተክርስትያኒቷ ትዘጋ›› የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

‹‹የገሀነም ደጆች አይችሏትም››

ጊዜው ወርሀ ክረምት ነው :: የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፆመ ፍልሰታ ወቅት ሲሆን በቤተክርስትያናችን ህግና ስርዓት መሰረት ይህ ጊዜ ዲያቆናት ፤ ካህናት መነኮሳት ፤ ጳጳሳት እና ምእመናን ለሐዋርያት የተገለፅሽላቸው እናታችን ለእኛም በምህረት አትለይን እያሉ በፆም ፤ በፀሎት ፤ በስግደት የሚለምኑበት ጊዜ ነው፡፡

ቦታው በሐረር መንገድ አዋሽ ሰባትን አልፈው ካለው የጉምሩክ የፍተሻ ጣቢያ ትንሽ ኪሎ ሜትር አለፍ ብሎ ከአሰቦት ገዳም መገንጠያ ሳይደርስ ከዋናው አስፋልት አንድ ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ የአባታችን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ሲሆን የቦታው ስም ቦርደዴ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ቤተክርስትያን የሚገኝበት ቦታ ላይ ከ30 የማይበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ሲገኙ በቁጥር ከ40 እና ከ50 እጥፍ ልቀው የሚገኙት ግን ሙስሊም ማህበረሰቦች ናቸው፡፡ ይህ ቦታ ለአንድ አፍታም ቢሆን ከነገር እና ከትንኮሳ እፎይ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ቦታ ድረስ ሄጄ በተመለከትኩበት ጊዜ እዚህ ቦታ ላይ ያለው የሙቀት መጠን ክረምት ሳይል በጋ ከ40 ድግሪ በላይ ስለሆነ ቆሞ ማስቀደስ እንደ እግዚሐብሔር መልካም ፍቃድ ፤ ምህረት ፤ ቸርነት እንጂ እንደ እኛ ብርታትና ጥንካሬ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡
ቤተክርስትያኒቷ አካባቢ ያሉት ምዕመና ጧፍ ፤ እጣን ፤ ዘቢብ እና ንዋየ ቅዱሳትን ማሟላት አቅሙ ስለሌላቸው ይህ ችግር የቀን ተቀን የውስጥ ችግር ችግራቸው ሆኖ አሁንም አሉ ፡፡ የባሰ አታም ነውና  አንድ ጊዜ ቅዳሴ ላይ ወንጌል ለማንበብ ጧፍ አልቆ በኩራዝ የተጠቀሙበት ጊዜም ነበር ፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ከአክራሪ ወገን የሚመደቡት የእስልምና ተከታዮች በአካባቢው ላይ ለ24 ሰዓት ያህል ከ4 በሚበልጡ መስኪዶቻቸውን ድምፅ ማውጫ Speaker ወደ ቤተክርስትያን አዙረው ‹‹አላህ ዋክበር›› በሚሉበት ሁኔታ ላይ ምንም ጥያቄ ያላቀረቡት በአካባቢው የሚገኙ  ክርስትያኖች በዓመት አንድ ጊዜ ለ16 ቀናት ብቻ ያለውን የሱባኤ ጊዜ ለሊት ሰዓታት እና ኪዳኑ ፤ ጠዋት ትርጓሜው እና ስብከቱ ፤ ከሰዓት ቅዳሴው ረበሸን ብለው ቤተክርስትያኒቷ እንድትዘጋላቸው  ለአካባቢያቸው ወረዳ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው መጠየቃቸውን አረጋግጠናል፡፡ ይህን ጥያቄ የመስተዳድሩ  ሃላፊ ከሰማ በኋላ ለሚቀጥለው ቀን የቀጠራቸው ሲሆን በሚቀጥለው ቀን ሲመጡ ምንም ምላሽ ስላላገኙ ሓላፊውን በኃይል ከቢሮ ያባረሩት ሲሆን ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው የክልሉ መንግስ ጋር እንደደረሰ ፤ አካባቢው ላይ የሚገኙ ክርስትያኖች ጉዳዩን ወደ ፊደራል መንግስት የወሰዱት ሲሆን መንግስት የዛኑ ቀን ማታ አካባቢው ላይ የሚገኙ ፌደራል ፖሊሶች ማታ 3፡00 አካባቢ ወደ አካባቢው በፓትሮል በመምጣት ይህን ጥያቄ የጠየቁትን ሰዎች ግማሽ ያህሉን ለቅመው ወስደው ወደ እስር ቤት የከተቷቸው  ሲሆን የተቀሩትን ግን ሸሽተው አምልጠዋል፡፡ መንግስት ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ሁኔታውን በጥቂቱ ያረጋጋ ሲሆን ፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው በፊደራል ፖሊስ  እየተጠበቀ ይገኛል::

እኛ በአሁኑ ሰዓት እንትና 18 ገፅ ወቀሳ ፃፈ ፤ ያኛው ሰባኪ አውደ ምህረት ላይ እንዳይቆም ተከለከለ ፤ በዚህ መፅሄት ላይ እንትና መልስ ሰጠ ፤ አንዱ ይቅርታ አለ ሌላኛው ይቅርታ ተቀበለ እያልን ስራ መስራት በሚገባን ወቅት ወሬ ስናራግብ ለቤተክርስትያን መሆን በሚገባን ሰዓት ጊዜያችንን እና አቅማችንን አልባሌ ቦታ ላይ በማዋልና ትርፍ የሌለው ስራ በመስት ላይ እንገኛለን፡፡

አሁንም ጊዜው አልረፈደም ስለ ጥቂት ሰዎች ማውራታችንን አቁመን ስለ ቅድስት ቤተክርስትያን ዘብ እንቁም ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ይህን የጠየቁ ሰዎች ነገ ምን ማድረግ እንደሚያስቡ ለማስረዳት መምህር ሊያሻን አይገባም፡፡

በዚች ምድር ላይ የምንቆየው እንደ ማቱሳላ 969 ዓመት አለመሆኑን አውቀን በኖርንበት፤በምንኖርበት  ጊዜ ሁሉ ከቤተክርስትያን ጎን ለመቆም ያብቃል፡፡

(ከአምደ ሃይማኖት)

ሐሰት አንናገርም፤ እውነትንም አንደብቅም
‹እግዚሐብሔር ቤተክርስትያንን ይጠብቅ ››

Friday, August 26, 2011

ዲያቆን ዳን ኤል ክብረት የዓለም የሰላም አምባሳደ ተብሎ በፕሬዘዳንት ግርማ ተሸለመ

(ምንጭ፡-አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2003ዓ.ም. 70ኛ ዓመት ቁጥር 342)

ቪዥን ኢትዮጵያ ፎረ ዲሞክራሲ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መልካም ዜጋን በመቅረጽ እና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያላቸውን አራት ግለሰቦች ሊቀ ዲሞክራት እና ስድስት ግለሰቦችን ‘’የዓለም የሰላም አምባሳደር’’ የሚል ማዕረግ ሰጥቷል፣ በዚህም የነገረ ቤተክርስቲያን ተመራማሪ እና ደራሲ የሆነው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ‘’የዓለም የሰላም አምባሳደር’’ የሚል ማዕረግ ሰጥቶቷል፡፡


 
ስነስርዐቱ ላይ በመገኘት ማዕረጉን የሰጡት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሲሆኑ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ‘’የዓለም የሰላም አምባሳደር’’ የሚል ማዕረግ ካገኙት ግለሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ ቪዥን ኢትዮጵያ ፎረ ዲሞክራሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ በስነስርዐቱ ላይ እንደገለጹት የተመረጡት ግለሰቦች በግልና በመንግስታዊ ተቋማት የላቀ ሥራ የሰሩ ናቸው፡፡ የዜጎች መብት እንዲታወቅ ና እንዲከበር ከፍ ያሉ ተግባራት አከናውነዋል አርአያና ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱም ናቸው ድርጅታችን ወደፊትም እንዲህ ያሉ ግለሰቦችንና ኃላፊዎችን ለተግባራቸው ዕውቅና በመስጠት የመሸለም ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ለአገልግሎት ባሕር ማዶ የሚገኘው ዲ/ን ዳንኤል ክብረትም በባለቤቱ አማካኝነት የማዕረግ ስጦታውን ተቀብሏል

የአቡነ አብርሃምና አቡነ ኤውስጣጤዎስ ጉዳይ

የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ወክለው በውጭ ገር ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወደ ገር ቤት እንዲመጡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተላከላቸው ታውል።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ሀገረስብከት የሚያሰተዳድሩ ሊቃነ ጳጳሳት ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር በአካል መገኘት አለባቸው።ነገር ግን የተወሰኑት ሊቃነ ጳጳሳት ባልታወቀ ምክንያት ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በጉባኤው ያልተገኙ መሆኑ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሆኖአል። በተለይም በአሜሪካን ገር ያሉት ብፁዕ አቡነ አብረሃም እና አቡነ ኤዎስጣቲዎስ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ እንጦንስ አዲስ አበባ በሚደረገው ርክበ ካህናት ጉባኤ ከተሳተፉ አምስተኛ ዓመታቸው ሲሆን ግንኙነታቸው በስልክ እና በፋክስ ቢቻ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ወደ ገር ቤት ለመሄድ ያለመፈለጋቸው ጉዳይ እቀየራለሁ ከሚል ስጋት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ ባለፈው ዓመት አቡነ አብረሃም በሌሉበት ከቦታቸው እንዲነሱ ሲወሰን በሰሜን አሜሪካ ያሉ ምዕመናን ባሰሙት ተቃውሞ እንዲቀጥሉ መደረጉ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጥቅምት 2004 ዓ፡ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሁሉም ከያሉበት እንዲመጡ ትዕዛዝ የተላለፈ ሲሆን በተለይም ከላይ ለተጠቀሱ አባቶች ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደደረሳቸው ለማወቅ ችለናል::አባቶችም የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ባንድነት ለመምከር እንደሚመጡ ይጠበቃል።

(ሰበር ዜና) አቡነ አብርሃምና አቡነ ኤውስጣቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተጠየቁ

መኖሪያቸውን አሜሪካ ያደረጉ አባቶች የአቡነ አብርሃም እና የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከቦታቸው መነሳት ዋነኛ አጀንዳ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ረቡዕ ነሐሴ 18 ቀን 2003 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ እንደሚያካሂድ ተገለጸ፡፡ ከስብሰባውም አጀንዳዎች ዋነኛው በዋሽንግተን እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና የሎስ አንጀለስ ና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት በቀንደኛ የተሐድሶ አራማጅነታቸው የሚታወቁትን ሊቀ ስዩማን ኃይለጊዮርጊስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ ልዩ ሹም” በማለት በቅዱስ ፓትርያሪኩ መሾማቸው ሲሆን ውሳኔውን እና ሹመቱን በመቃወም ሁለቱም ሊቃነ ጳጳሳት የተቃውሞ ድብዳቤ መጻፋቸው ነው፡፡ የተቃውሞው ይዘት ቃለ አዋዲው እና ቀኖና ቤተክርስቲያን ተጥሷል የሚል ሲሆን በአንድ ሀገረ ስብከት የሁሉም የበላይ ሊቀ ጳጳሱ መሆን ሲገባው ከሊቀ ጳጳሱ በላይ “ልዩ ሹም” መሾም ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ በዚህ ተቃውሞም የተነሳ ዛሬ በሚደረገው የቋሚ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ሁለቱንም ሊቃነ ጳጳሳት ከቦታቸው በማንሳት ወደ አገር ቤት አንዲሄዱ ሊወሰን እንደሚችል ቤተ ክርስቲያኒቱ ገለጸች።

ማህበረ ቅዱሳንና አቡነ ጳውሎስ በመስማማት ላይ ናቸው


የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ከማኅበረ ቅዱሳን አመራር ጋር ውይይት አደረጉ አትም ኢሜይል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢተዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከማኅበረ ቅድሳን ሥራ አመራርና አስፈጻሚ ጉባኤያት ተወካዮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ስለ ማኅበሩ አገልግሎትና በተለይም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት በተካሔደው ውይይት፤ የማኅበሩ አመራር ስለተሐድሶ መናፍቃን እንቅቃሴ አራማጆችና ተቋማት የተዘጋጁ ልዩ ልዩ መጻሕፍት እንዲሁም በምስል ወድምጽ /VCD/ የታገዘ ገለጻና ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት ከተመለከቱ በኋላ “ይህ ሁሉ የንብ ሠራዊት እያለ ወረራው ሲካሔድ የት ነበራችሁ?” የሚል የአባትነት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር መጠበቅ የሁሉም ሓላፊነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚህም በላይ መብታችንን በሕግ ሳይቀር ማስከበር እንደሚኖርብን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በልጅነት ደረሻው እያከናወነ ያለው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ “ተሐድሶ ናቸው” ማለት ግን አግባብ እንዳልሆነና ይህም የቤተ ክርስቲያናችንን አሠራር ጠብቆ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የማኅበሩ አመራር አባላትም፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ሥራ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነት፣ በእንዴት ዓይነት ሁኔታና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምእመናን ግንዛቤ አግኝተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ፤ እንዲሁም ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የሚመሩና የሚደግፉ ተቋማትን፣ ስልትና አሠራራቸውን የማሳወቅ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ1990 ዓ.ም የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ የማጋለጥ ሰፊ ሥራ ባከናወነበት ወቅት፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ነገር ግን ፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ በምእመኑ ውስጥ በመዝራት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው “መነኮሳት” ተወግዘው እንዲለዩ ሲደረግ፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐትና አሠራር መሠረት ማኅበሩ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ ለሊቃውንት ጉባኤ አቅርቦ ከዚያም በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረገበት ሁኔታ እንደነበረ፤ የማኅበሩ አመራር አባላት በውይይቱ ላይ አስታውሰው፤ ማኅበሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር ጠንቅቆ እንደሚያውቅና ይህንኑ ለማስጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ማኅበረ ቅዱሳን እየሠራ ያለው የግለሰቦችን ስም በመጥቀስ “ተሐድሶ” የማለት ሳይሆን፤ ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምንነትና ስልት ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ምእመናን ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማሳወቅ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ወደፊትም በዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና ሥራ ላይ የተጠመዱ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ የሚገኙ አካላትንና ደጋፊዎችን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐትና አሠራር በመጠበቅ ማኅበረ ቅዱሳን ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትና አባቶች እንደሚያቀርብ በማኅበሩ አመራር አባላት ለቅዱስነታቸው ተገልጿል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩም፤ በበቂ መረጃ በማስደገፍ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አካል በማቅረብ ሁሉም ነገር በሕግና በሥርዐት መከናወን እንዳለበት አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስለ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ ጉዳይ በሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ሰላም የሰጠው ቃለ ምልልስ

ስለ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ያስተላለፈውን መልዕክት እነሆ!!! ምንጭ (ደጀ ሰላም)

ስለ ተሐድሶ እና ተያያዥ ጉዳዮች የዘሪሁን ሙላቱ ቃለ ምልልስ


“የሃይማኖታችን ጉዳይ የፓትርያርኩ ብቻ አይደለም” የሚለው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ከቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ  የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ መለኮት፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በፊሎሎጂ ትምህርት ተመርቋል። በአሁኑ ወቅትም ደግሞ የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ) ጥናቱን በማገባደድ ላይ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ወቅታዊ ሁኔታ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትከተለው አስተምህሮ ዙሪያ ከዕንቁ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
 
 
ከዚህ በታች ያለውን ሙሉ ቃለ መጠይቁን እንድታነቡ በአክብሮት እንጠይቃለን!!!

ብፁእ አቡነ ሚካኤል አረፉ

ስለ "ብፁዕ አቡነ ሚካኤል" የማ/ቅዱሳን ዘገባ

(Mahibere Kidusan):- የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ነሐሴ 8 ቀን 2003 ዓ.ም አርፈዋል። በአንብሮተ ዕድ ከተሾሙበት ከነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ በአሁኑ ሀገረ ስብከታቸው የተሾሙ ሲሆን በመካከል ለተወሰኑ ወራት የወላይታ፣ ዳውሮና ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።

የሐሞት ጠጠር ሕመም የነበረባቸው ብፁዕነታቸው የቀዶ ጥገና ሕክምናቸውን በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በመከታተል ላይ የነበሩ ሲሆን በመካከል ከሰመመናቸው መንቃት ሳይችሉ እንደቀሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ቀጣይ የአስከሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ምክንያቱ ሊገለጽ እንደሚችልም ይገመታል።

በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የተሾሙት የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት አባ ተክለ ሚካኤል ዓባይ አሁን ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በቀድሞው አድዋ አውራጃ በዓምባ ሰነይቲ ወረዳ በላውሳ ቅዱስ ገብርኤል አካባቢ ከአለቃ ዓባይ ወ/ገብርኤልና ከወ/ሮ ታደለች ንጉሤ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

በታላቁ በደብረ ዓባይ ገዳም ከመምህር አበራና ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ከመሠረተ ትምህርት እስከ ጸዋትወ ዜማ፣ ከመምህር የኔታ የኋላእሸት መዝገበ ቅዳሴ ጠንቅቀው ከተማሩ በኋላ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

በዋልድባ ገዳም መዓርገ ምንኩስና ተቀብለዋል፡፡ ጎንደር ክፍለ ሀገር በወገራ አውራጃ በጉንተር አቦ ከመሪጌታ ሐረገወይን፣ ጎንደር ከተማ ከመምህር እፁብ ቅኔ ተምረው ተቀኝተዋል፡፡

በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እያገለገሉ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት በአዳሪነት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በውጪ አገር እንግሊዝ ለንደን ሴንት ኤድዋርድስ ኮሌጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለአንድ ዓመት፣ ግሪክ አገር በአቴንስ ዩኒቨርስቲ ለስድስት ዓመታት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር በቲኦሎጂ ማስትሬት ዲግሪ፣ በአሜሪካ ሆሊ ክሮስ በተባለው የግሪክ ሴሚናሪ ከሲስተማቲክ ቲኦሎጂ ዲፕሎማ፣ በቦስተን ዩኒቨርስቲ የኤስ.ቲኤም ወይም በፓስተራል ካውንስሊንግ /ሳይኮሎጂ/ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የእስኮላር ሽፕ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ ገዳማት መምሪያ ኃላፊ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ዲን፣ በወቅቱ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የዕቅድና ጥናት መምሪያ ኃላፊ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ሐላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ ነሐሴ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና እንግዶች እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።